በጉራጌ ዞን የመስህብ ሥፍራዎችን በማልማትና በማስተዋወቅ የተጀመሩ ተግባራት ውጤት እያመጡ ነው
ወልቂጤ፤ ጥቅምት 5/2018(ኢዜአ):- በጉራጌ ዞን የቱሪዝም መስህብ ሥፍራዎችን በማልማትና በማስተዋወቅ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ የተጀመሩ ተግባራት ውጤት እያመጡ መሆኑን የዞኑ ባሕልና የቱሪዝም መምሪያ አስታወቀ።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ መሠረት አመርጋ፤ ዞኑ ካላው እምቅ የቱሪዝም አቅምና መዳረሻዎች አንፃር ይገኝ የነበረው ጥቅም አነስተኛ ሆኖ መቆየቱን አስታውሰዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህን መቀየር የሚያስችል ሥራ በተቀናጀና ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም በዞኑ ያሉ የተፈጥሮ፣ ሰው ሰራሽናና ታሪካዊ የመሥህብ ሥፍራዎችን በማልማትና በማስተዋወቅ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ማሳደግ መቻሉን ገልጸዋል።
በተለይም በዞኑ ያሉ የቱሪዝም መሥህቦችን ለማስተዋወቅና ለማስጎብኘት ከግሉ ዘርፍ፣ ከመገናኛ ብዙኃንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መሰራቱ ውጤት እያመጣ መሆኑን ተናግረዋል።